Fana: At a Speed of Life!

ኢሬቻ ለህብረ ብሔራዊ አንድነታችን የነገ ተስፋ የብርሃን ጮራ ነው – አቶ ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢሬቻ ለህብረ ብሔራዊ አንድነታችን የነገ ተስፋ የብርሃን ጮራ ነው ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

የኢሬቻ በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ የምስጋናና የፍቅር፣ የደስታ፣ የሰላም፣ የእርቅ፣ የወንድማማችነት እና እህትማማችነት ተምሳሌት ነው ብለዋል።

በመሆኑም ኢሬቻ ለህብረ ብሔራዊ አንድነታችን የነገ ተስፋ የብርሃን ጮራ ነው በማለት ገልጸው፤ ኢሬቻ የኦሮም ህዝብ ጭጋጋማውን ክረምት ወቅት አልፎ በሰላም ወደ አዲሱና የብርሃን ተስፋ ወደያዘው ዓመት በሰላም ላሸጋገረ ለፈጣሪ ”ዋቃ” ምስጋና የሚያቀርብበት በዓል ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ኦሮሞ ህዝብ ችግር ሲገጥመው አቤቱታውን የሚያቀርበው “ለዋቃ” ነው፤ በደስታ ጊዜም ተሰብስቦ “ዋቃ”ን ያመሰግናል ብለዋል።

ኢሬቻ በበዓሉ የተገኙት ሁሉ ይቅር የሚባባሉባት፣ ፀበኞች የሚታረቁበት፣ ቂምና ቁርሾ የሚተውበትና የተጣላ ይቅርታ የሚደራረጉበት ድንቅ የሆነ የሰላም ግንባታ ተምሳሌት በዓል ነው በማለት ገልጸዋል።

በኢሬቻ በዓል ላይ የግል ወይንም ቡድናዊ ፍላጎት እንደማይንጸባረቅ ገልጸው፤ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት ደማቅ ባህላዊ ክዋኔ የሚታይበት ብቻም ሳይሆን ልምላሜ የሚወደስበት ልማት ለማፋጠን ሁላችንንም በአንድነት ለማስተሳሰር እምቅ አቅም ያለው ባህላዊ ትውፊት ነው ብለዋል።

ከኢሬቻ በዓል ዕሴቶች ብዙ በመማር ያሉንን አቅሞች አሰባስበን ተስፋን መያዝ ያሰፈልጋል በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የምስጋና፣ የእርቅ፣ የሠላምና የአንድነት በዓል ከሆነው ኢሬቻ በመማር ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ኢሬቻ ትምህርታዊ ፋይዳዉ የላቀ በመሆኑ ጠብቆና ተንከባክቦ ለትዉልዱ ማስተላለፍና በህብረብሔራዊ አንድነታችን መሀል ማስረፅ ይገባል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.