Fana: At a Speed of Life!

ኢሬቻ የማህበራዊ መስተጋብር ማስተሳሰሪያ ገመድ ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢሬቻ ለኦሮሞ ህዝብ ባህሉ፣ ትውፊቱ እና እሴቱ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገልጸዋል::

ርዕሰ መስተዳድሩ ለ2017 የኢሬቻ በዓል ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳቹ መልካም ምኞት መግለጫ መልዕክታቸው፤ ኢሬቻ የማህበራዊ መስተጋብር ማስተሳሰሪያ ገመድ ነው ብለዋል፡፡

ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ለተደረገለት መልካም ነገር ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት እና እርቅን የሚያወረድበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት የተከበረ በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

የኦሮሞ ህዝብ ለዘመናት ጠብቆ እና ተንከባክቦ ያቆየው የኢሬቻ በዓል፤ ህዝቦ የሚታወቅበት መለያ እሴቱ መሆኑን ተናግረዋል።

ወደ ቀደመው እሴታችን በመመለስ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የፖለቲካ ስብራቶቻችንን ለመጠገን በከፍተኛ ሁኔታ እየሰራን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዚህም በርካታ ድሎችን አስመዝግበናል ብለዋል፡፡

በተሰሩ መልካም ስራዎች ቡሳ ጎኖፋን ስራ ላይ በማዋል ማህበረሰባችን እርስ በርስ እንዲተጋገዝ፣ እንዲረዳዳ እና አንዱ ለአንዱ እንዲቆም አስችለናል ብለዋል፡፡

ለትምህርት ዘርፍ ትኩረት በመስጠት ትውልዱ ግብር ገብነትና የሀገር ወዳድነትን እንዲያዳብረ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የማህበረሰቡ የቀደሙ እሴቶች እንዲመለሱ ተሰርቷል ሲሉ ገልጸዋል።

በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በሀገራቸው መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አስተላልፈዋል።

እየተገኙ ያሉ ስኬቶች በዘፈቀደ የመጡ ሳይሆን ዘመናዊ የአመራር ጥበብን በመከተል እና ተግዳሮቶች በፅናት በማሸነፍ እንደሆነ ገልጸው፤ ወደ ቀደመው ድንቅ እሴታችን በመመለስ ለላቀ ሀገራዊ ስኬት ከመንግስት ጎን በመሆን መረባረብ ይገባል ብለዋል።

በመጨረሸም ለመላው የኦሮም ህዝብ እና ለበዓሉ ታዳሚዎች እንኳን ለኢሬቻ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት በዓሉ የሰላም እና የደስታ ይሁንልን ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.