Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ2017 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ ሙሉ መልዕክት

የተከበርከው የኦሮሞ ሕዝብ ሆይ

እንኳን አስቸጋሪውን የክረምት ወቅት አልፈህ ለብሩሁ ብራ ተሸጋገርክ!

ኢሬቻ ዕርቅ ነው፤ ፈጣሪ ደግሞ ዕርቅ ይወዳል። የተጣሉ ሰዎች ቂም ይዘው ለኢሬቻ ወደ መልካ አብረው አይወርዱም። ኢሬቻ መትረፍረፍ ነው! ኢሬቻ ምስጋና ነው! ኢሬቻ ልምላሜ ነው!

ለምለም ሣር ክብርን ፣ ፍቅርን እና መልካም ምኞትን ይወክላል። ብራ ሽግግር ነው፤ ያለፈውን ወደኋላ ትተን ወደ አዲስ ተስፋ በንጹሕ ኅሊና እንሻገራለን። ከሕዝቡ እሴት ውስጥ ጎልቶ የሚታየውም ይህ ነው። ኢሬቻ አንድነት ነው። ኢሬቻ ኅብረት ነው። ከኢሬቻው መልካ የሚቀርም ሆነ ወደ ኋላ የሚል የለም። አባቶችና እናቶቻችን አቆይተው ያወረሱን እሴት ማዳላት የለውም። ሰው ሁሉ እኩል ነው። “ሰብአዊነት ከሰው ውጪ ትርጉም የለውም” ብሎ ነው ኦሮሞ የሚያምነው። ኦሮሞ እና አብረውት የሚኖሩ ሌሎች ሕዝቦችም ፈጣሪ ባበጀው መልካና ወንዝ ላይ ይሰባሰባሉ። ይህ ደግሞ ወንድማማችነት ነው። ኢትዮጵያ የምትታወቅበት ብዝኃነት በመልካ ኢሬቻ ላይ ይታያል። ይህ ደግሞ የሀገራችን ሕዝቦች እርስ በእርስ ያላቸውን መቀባበል እና መከባበር እንዲሁም መልካም ምኞት ለዓለም ማኅበረሰብ የሚያሳይ ነው። ወንድማማችነታችን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም ነው። ከሌላ የወሰድነው ሳይሆን የተወለድንበት ነው ። ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያደግንበትና የኖርንበት ነው። ከውጭ እንደሚያዩን ሳይሆን በውስጣችን ከብረት የጠነከረ አንድነት አለ። አንድ ላይ ከቆምን፣ የእኛን መፍረስ ሲያሟርቱ የሚውሉትን ማሳፈር እናውቅበታለን።

ታሪካችንም ይህንኑ ያሳያል። ኦሮሞ ከሌሎች ፍጥረታት አንድነት ጋር እያነፃፀረ ፈጣሪውን ሲለምን ፦

“ ፈጣሪ ሆይ፣

ሠርተህ አታፍርሰን፣

ከለላ አታሳጣን፣

ልባችንን ከድንጋጤ ፣

ዓይናችንን ከዕንባ ታደግ ።

ከመለያየት ታደገን፣ እንደዛፍ አጽንተህ አቁመን!”

በማለት ፈጣሪውን ይለምናል። እንደዛፍ ተተክሎ የጠነከረና ሥር የሰደደ አንድነት ስጠኝ በማለት ወደ ፈጣሪው ይጸልያል። በዚህ ጸሎት ውስጥ ከሁሉም በላይ የሆነው ፈጣሪ አለ። ሰፍ (ሌላውን ማክበር) አለ። ፍጥረት አለ። የሰው ልጅ ከፈጣሪ ጋርና ከሌሎች ፍጥረታት ጋር ያለውን ግኑኝነት ከዚህ ወደ ፈጣሪ ከሚደረግ ጸሎት እንገነዘባለን።

ኦሮሞ የጊዜ ቀመርን/ዑደትን በራሱ ያውቃል። የከዋክብትንና የጨረቃን ዑደት በመቁጠር በዓላትን ያሰላል። ይህ ልዩ ስጦታ ነው። የክዋክብትን ዑደት ማወቅ መመራመርን ይጠይቃል፤ ሥልጣኔን ይጠይቃል። አርቆ በማሰላሰል ለሌላው አቅርቦ ማስገንዘብን ይጠይቃል። የክዋክብትን ዑደት ማወቅ ቀናትን ማወቅ ነው፤ ወራትን ማወቅ ነው፤ ዘመኑንና ገዳውን ማወቅ ነው፤ ታሪክንና ሁነትን ማወቅ ነው። በጋን እና ክረምትን ማወቅ ነው። የፈጣሪን ኃይልና የሚገባውን ምስጋናም ማወቅ ነው። ኦሮሞ ከልምድ ያካበተው ቱባ ዕውቀት እንደ አየር ሁኔታ ትንበያ ባለሞያ ወቅቶችን በመለየት እንደየባህሪያቸው አብሮ እንዲኖር ረድቶታል። ኦሮሞ የጨረቃና የክዋክብትን ግንኙነት የሚረዳበት ጥበብ አለው። ቅደም ተከተላቸውንና አሰላለፋቸውን በማየት ያለፈውን ነገር ይተነትናል፤ መጪውን ይተነብያል። የጊዜ ዑደት ይህን ዕውቀት ይጠይቃል። የገዳ ሥርዓት የዚህ የጊዜ ዑደት ውጤት ነው። የልቡና ዓይን ወይንም የአስተውሎት ውጤት ነው።

ስለመቸገር እና መትረፍረፍ፣ ስለ እንስሳትና ሀብት ማፍራት፣ ስለ ኑሮና ሕይወት፣ ከሌሎች ጋር ስለመኖር ግኑኝነትና ጉርብትና፣ ስለ አንድነትና ኅብረት፣ ስለ እውነትና ስለ ሰብአዊነት ሁሉ በወጉ ደንግጎ ያስቀመጠ ሥርዓት ነው። እንዲህ ያለው ሥርዓት ከራዕይ ውስጥ የሚቀዳ እንጂ በአንድ ጀምበር የሚረጋገጥ አይደለም።

የትናንቱ ሥልጣኔ መርሕ ዛሬም ያስፈልገናል። አሻግሮ የሚያይና ረጅሙን የምናሳጥርበት ሐሳብ ዛሬም እጅጉን ያስፈልገናል።

ገዳ የአስተውሎት ውጤት ነው። ኦሮሞ የቸገረውን ነገር የሚፈታበትና ዘመን የማይሽረውን ጠንካራ ሥርዓት በአስተውሎት በማበጀት ተጠቅሞበታል። ጎረቤቶቹ ሆነው የሚኖሩ ወንድሞቹ ከዚህ አስተዋይነቱ ተጠቅመዋል። ገዳ ምርጫን በስምንት ዓመት በማድረግና የሥልጣን ጊዜን በመገደብ በፈቃደኝነትና በሰላም ሥልጣንን መረካከብን አስተማረ።

ከአንድ ምዕራፍ ወደ ሌላ ለመሻገር የዝግጅት ጊዜ እንደሚያስፈልግ አስቀመጠ። የኃላፊነትን ሥልጣን በየዘርፉ፣ በዕድሜና በጾታ በመከፋፈል፣ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ሁሉንም በማሳተፍ ወደ ኅብረተሰቡ የመቅረብ መደበኛ አሠራርን በማስቀመጥ፣ ማኅበራዊ አንድነትንና ሰላምን በማስከበር ውስጥ ሁሉም ዜጋ ድርሻ እንዳለው ደነገገ።

ይህ የአስተውሎት ውጤት ነው፤ የንቃት ውጤት ፤ የመገንዘብ ውጤት ነው፤ የመተንተን ውጤት ነው።

እኛ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፋይዳ በሌላቸውና ማንም ተነሥቶ የግሉን እና የቡድን ፍላጎቱን ለማሳካት የሚያቀብለን አጀንዳ ላይ ጉልበታችንን ከመጨረስ ወጥተን፣ በዋናው ጎዳናችን ላይ እናተኩር። ክብርንና ፍቅርን ይዘን ድህነትና ችግር አውልቀን እንጣል። ወደ ብልጽግና መልካ እንገሥግሥ።

ያመለጠ ዕድል ድጋሚ አይገኝም። ለዚህ ትውልድ ያለን ዕድል አሁን ነው። በተገኘው ዕድል የሀገራችንን መጪ ጊዜ አሁኑኑ ማበጀት አለብን። እንደ አባቶቻችን ትልቅ የማስተዋል ጉልበት ያስፈልገናል። የወደቀ ሐሳብ ይዘን መደነቃቀፍ ለውድቀት ካልሆነ ወደፊት የምንወነጨፍበት ጉልበት አይሆነንም።

አባታቾቻን ከዚህም ከዚያም ጩኸትና ትችት ስለበረከተ የገነቡትን ሥርዓት አልጣሉትም። እኛም እንዲሁ ነን፤ ማንም በውሸት ከዚህም ከዚያም ተቀባብሎ በመጮህ በውሸት ጩኸት ቢረዳዳም የያዝነውን ነገር ከግብ ሳናድርስ አንቀርም። የተሰጠን አደራ አለ ። የተሰጠንን አደራ ይዘን የጀመርነውን በስኬት እናጠናቅቃለን። ብዙ ወጣቶችን አጥተንበት አደራ አንበላም። ሀገራችን ኢትዮጵያ እውነት አላት። ካለፈው መልካም ነገር እንወስዳለን፤ ያለፈው የሚወቀስበትን እያስተካከልን እንዳንወቀስ አድርገን እንሠራለን። የሰውን ልጆችን በእኩል ማየትን ከገዳ እንማራለን። አሁንም ትልቅ አስተውሎት ያለው ይህ ሕዝብ ለኢትዮጵያ የተሻለ ነገር በመፍጠር ከሌሎች ወገኖቹ ጋር ታላቋን ኢትዮጵያ ይገነባል።

እንኳን ለ2017 የኢሬቻ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

ገዳው የበረከት ይሁንልን!

ዘመኑ የብልጽግና ይሁን!

ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር!

መስከረም 24፤ 2017

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.