Fana: At a Speed of Life!

ኢሬቻ የአንድነት ምልክት በመሆኑ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ እየተሰራ ነው- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢሬቻ የአንድነት ምልክትና የሰላም ተምሳሌት በመሆኑ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ እየተሰራ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

6ኛው የኢሬቻ ፎረም በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ “ኢሬቻ ለባህላችን ሕዳሴ” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ነው።

አቶ ሽመልስ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ኢሬቻ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበትና ሰዎች ያለምንም ልዩነት የሚሳተፉበት በዓል ነው።

ኢሬቻ የሕዝቦች አንድነት የበለጠ የሚጠናከርበት በመሆኑ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲሸጋገር በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ኢሬቻ የምስጋና፣ የሰላም፣ የይቅርታ፣ የአብሮነትና የወንድማችነትን እንዲሁም ባህላዊ እሴቶች የሚንጸባረቁበት በዓል መሆኑን አውስተዋል።

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ አዲስ አበባ በኮሪደር ልማት አምራና ተጨማሪ ውበት ተላብሳ ሆረ ፊንፊኔን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

የለውጡ መንግሥት ሕዝቡን አንድ በማድረግ አዲስ አበባ ተለውጣ የዓለም የቱሪስት ማዕከል እንድትሆን ማድረጉን ጠቅሰው፤ በአዲስ አበባ ለተመዘገበው ለውጥ የተጉትን አካላት ሁሉ አመስግነዋል።

መንግሥት የገባውን ቃል ወደ ተግባር ለውጦ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በማከናወኑ በህዝብና በመንግስት መካከል ያለው መተማመን ማደጉን ገልጸዋል።

ሰላም፣ ፍቅር እና አንድነትን እውን ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘን መትጋት አለብን ያሉት ከንቲባዋ፤የኢሬቻ በዓል በድምቀት እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.