የተሻለ የኦዲት አፈጻጸም ላስመዘገቡ መስሪያ ቤቶች ዕውቅና ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስቴር የተሻለ የኦዲት አፈጻጸም ላስመዘገቡ 12 የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የዕውቅና ሽልማት መስጠቱን አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ የውስጥ ኦዲት ስራዎችና በፌዴራል የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የ2015 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝት አፈጻጸም ላይ የሚመክር መድረክ አዘጋጅቷል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ በመድረኩ እንደገለጹት÷ በ2015 በጀት ዓመት ነቀፌታ የሌለው የኦዲት አስተያየት ያገኙ ተቋማትን 53 በመቶ ማድረስ ተችሏል።
የፋይናንስ ዘርፉን የአሰራር ስርዓት በማዘመን ውጤታማ፣ ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን ህጎችን በማውጣት፣ ስልጠናዎችን በመስጠትና ክትትል በማድረግ ተቋማቸው ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በሚኒስቴሩ የኢንስፔክሽን መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ አባይነሽ ተሾመ በበኩላቸው÷ በተከናወኑ ስራዎች የፌዴራል መስሪያ ቤቶች በተለይም የኦዲት ችግር ይስተዋልባቸው የነበሩ ዩኒቨርሲቲዎች በዕቅድ የመመራትና በወቅቱ ሪፖርት የማድረግ አፈጻጸም እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ በ2015 በጀት ዓመት ነቀፌታ የሌለበት የኦዲት ሪፖርት በማስመዝገባቸው የእውቅና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።
ከነዚህ መካከል የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የሠላም ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ፣ የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን እንደሚገኙበት የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
እንዲሁም የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን፣ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት፣ የፖሊሲ ጥናት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት፣ ጂንካ እና ቦንጋ ዩኒቨርሲቲዎች ሽልማት ከተሰጣቸው ውስጥ ይገኙበታል፡፡