የፌዴራል ፖሊስ የኢሬቻ በዓልን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ በዓል ያለምንም ችግር በድምቀት እንዲከበር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል አስታወቁ፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የኢሬቻ በዓል አከባበርን በተመለከተ ከአባ ገዳዎችና ከሀደሲንቄዎች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በዚህ ወቅት÷ በዓሉ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር በሰው ኃይል፣ በሎጂስቲክስና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እየታገዘ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል፡፡
የኢሬቻ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ የአባገዳዎችና የሀደሲንቄዎች ሚና ከፍተኛ ነው ማለታቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ሰላምና ፀጥታን ለማስከበር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፀጥታና ደኅንነት አካላት ጋር በመቀናጀት በተካሄዱ ኦፕሬሽኖች የበዓሉን ድባብ ለማጠልሸት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ከታጠቁት ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎች ጋር በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡