የእንዶዴ ሎጂስቲክስ ማዕከልን ለማልማት ከአፍሪካ ልማት ባንክ ተወካዮች ጋር ውይይት ተደረገ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) የእንዶዴ ሎጂስቲክስ ማዕከልን በመንግስትና የግል ሴክተር አጋርነት በማልማት የኢትዮጵያን የሎጂስቲክስ አገልግሎት ለማሳደግ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም÷ እየጨመረ የመጣውን የወጪ ገቢ ጭነት ለማስተናገድ የሚያስችሉ የወደብ ማስፋፊያ ስራዎችን በመስራት ኢትዮጵያን የሎጂስቲክስ ማዕከል ለማድረግ በስፋት እየተሰራ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
በውይይቱ የእንዶዴ ሎጂስቲክስ ማዕከልን ለማልማት የተዘጋጀ የትብብር ፕሮጀክት ቀርቦም ውይይት መደረጉን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ ተወካዮች የኢትዮጵያን የሎጂስቲክስ አቅም ለማሳደግ እየተሰራ ያለው ስራ የሚበረታታ መሆኑን አንስተው፤ በቀጣይ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ በመወያየት በጋራ መስራት የሚቻልባቸው ሁኔታዎችን እንፈጥራለን ብለዋል፡፡
በውይይቱ የሚኒስቴሩ አመራሮች፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡