ኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በድምቀት እንዲከበር ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ስራ መገባቱን ጥምር የፀጥታ ሀይሉ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጪው ቅዳሜ የሚከበረው የ2017 ዓ.ም ኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል ትውፊቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ጥምር የፀጥታ ሀይሉ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን አስታውቋል፡፡
የፀጥታ አካላቱ ለሚያከናውኗቸው ተግባራት በተዘጋጀው ዕቅድ ላይ ውይይቱ ሲካሔድ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ም/ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ߹ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ውይይቱን መርተውታል፡፡
በውይይቱ÷ በዓሉ ባህላዊ ስርዓቱን ጠብቆ እንዲከበር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የፀጥታ ሀይል ተሰማርቶ ወደ ስራ መግባቱ ተገልጿል፡፡
የበዓሉን ገፅታ የሚያጠለሽ እና ግጭት ቀስቃሽ ጽሁፎችና መልዕክቶችን እንዲሁም ከበዓሉ ጋር ግንኙነት የሌለውን ቁሳቁስ ወደ በዓሉ ማክበሪያ ስፍራ ይዞ መምጣት የተከለከለ ነው ተብሏል፡፡
በዓሉን ለእኩይ ዓላማ ለመጠቀም የሚደረጉ ማንኛውም ዓይነት ሕገ-ወጥ ተግባራት ተቀባይነት እንደሌላቸውና ይህንን ለማድረግ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ተጠቁሟል፡፡
በዓሉ በሰላም እንዲከበር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን የጠቀሰው ጥምር የፀጥታ ሀይሉ÷ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የአሰሳ እና ፍተሻ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ አመልክቷል።
ህብረተሰቡ የፀጥታ አካላቱ ለሚያከናውኑት የፍተሻ ስራ ተባባሪ እንዲሆንም አሳስቧል፡፡
በዓሉ በድምቀት ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል የፀጥታ ሃይሉን በማገዝ ሃላፊነታቸውን የሚወጡ የከተማዋ የሰላም ሰራዊት አባላት እና ባለድርሻ አካላት በተግባሩ ላይ እንደሚሳተፉ ተጠቁሟል፡፡
ከተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ህዝብ በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማዋ እንደሚገባ ታሳቢ በማድረግ ህብረተሰቡ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን በመቆም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥምር የፀጥታ ሐይሉ ማሳሰቡን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
ለሰላም እንቅፋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲያጋጥሙ በ011-1-26-43-59 ፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም መልዕክት ተላልፏል፡፡