ኢሬቻ የመከባበር እሴትና የትውልድ ቅብብሎሽ የሚታይበት በዓል ነው – ሃደሲንቄዎች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢሬቻ በዓል የመከባበር እሴት እና የትውልድ ቅብብሎሽ የሚታይበት መሆኑን ሃደሲንቄዎች ተናገሩ።
ሃደሲንቄ ዘውዲቱ ጌታቸው እንዳሉት÷ በኢሬቻ እሴት መሰረት የበዓሉ አከባበር ሥነ-ሥርዓት የትውልድን ቀጣይነት እና ቅብብሎሽ በሚያሳይ መልኩ ይከናወናል።
በዓሉ በሚከበርበት ቦታ በሚከናወነው ስርዓት በቅድሚያ ልጃገረዶች ከፊት የሚመሩ ሲሆን÷ በመቀጠል ሃደሲንቄዎች እንዲሁም ሴት አዛውንቶች ተከታትለው ይጓዛሉ፡፡
ከእነሱ ቀጥሎ አባገዳዎች በረድፍ እንደሚሄዱና ከእነሱ ቀጥሉ ፎሌዎች ከዛም ሌሎች ይከተላሉ ብለዋል።
ኢሬቻ የእርቅ፣ የሰላምና የአብሮነት መድረክ መሆኑን በመጥቀስ ሰላም በማውረድ በኩል ደግሞ ሴቶች ቀዳሚ በመሆናቸው ትልቅ ቦታ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።
ሃደሲንቄዎች ‘መሬሆ’ ዞሮ መጣን፣ ‘አራሮ’ እባክህ ታረቀን እያሉ ለፈጣሪ ምስጋና እና ውዳሴ እያቀረቡ ከፊት ይመራሉ ሲሉ ገልጸዋል።
በገዳ ሥርዓት ውስጥ እናቶች ይከበራሉ አስታራቂ ናቸው፤ በዚህ ምሳሌ ነው ሴቶች በኢሬቻ በዓል ላይ ከፊት የሚመሩት ያሉት ሀደሲንቄ ዘውዲቱ፤ በዓሉ ሁሉም ምንም ልዩነት ሳይገድበው የሚሳተፍበት መሆኑን አብራርተዋል።
ሃደሲንቄ ጫልቱ ኢብሳ በበኩላቸው÷ ኢሬቻ የሀገር ዓርማና ብዙዎችን የሚያሰባስብ በዓል መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
የኢሬቻ በዓል ፈጣሪ በፈጠረው መልካ ላይ ከጭለማ ወደ ብርሃን ላሸጋገረን አምላክ ምስጋና የሚቀርብበት ነው በማለት ገልጸው፤ የፍቅር፣ የሰላም እና እርቅ በዓል በመሆኑ በዕለቱ ሃደሲንቄዎች ሰላም እንደሚያውጁ ተመላክቷል፡፡