Fana: At a Speed of Life!

የ10 ወር ሕፃን ለማገት የሞከረችው ግለሰብ በ13 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጣች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በባህር ዳር ከተማ የ10 ወር ሕፃን ለማገት የሞከረችው ግለሰብ በ13 ዓመት ፅኑ እስራት መቀጣቷ ተገለፀ፡፡

ወጣት ትዕግስት አለነ የተባለች ግለሰብ መስከረም 7 ቀን 2017 ዓ.ም በባህርዳር ከተማ ቀበሌ 14 አካባቢ በቤት ሰራተኝነት ስራ መቀጠሯንና አሰሪዎቿም በዕለቱ የ10 ወር ሕፃን ልጃቸውን አምነው ሰጥተዋት ወደስራ መሄዳቸው ተገልጿል፡፡

ግለሰቧ አደራዋን በመብላት እና ያልተፈለገ ጥቅም ለማገኘት በማሰብ ስራ በጀመረችበት ዕለት ከቀኑ 10ሰዓት አካባቢ ሰው አለመኖሩን ካረጋገጠች በኋላ ሕፃኑን ይዛ መሰወሯ ተመላክቷል፡፡

የሕፃኑ ወላጅ አባት አቶ ወርቁ ሰማ ጉዳዩን አውቀው አዳሩን ሙሉ ሲፈልጉት ማምሸታቸውንና ለፖሊስ ከጠቆሙ በኋላም በማህበራዊ ሚዲያ አፋልጉኝ በማለት የልጃቸውን ፎቶ ማጋራታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከዚያም ግለሰቧ ለሕፃኑ አጎት ደውላ የ100 ብር ካርድ እንዲልክላትና ሕፃኑም እሷ ጋር መሆኑን ተናግራ ካርዱ ከተላከላት በኋላ በፅሁፍ መልዕክት 500 ሺህ ብር ዛሬውኑ ካላመጣ ህፃኑን እንደማያገኘው መናገሯ ተገልጿል፡፡

አባትም ይህን ያህል ብር እንደሌለው እና ለጊዜው 47 ሺህ ብር እንዳለው ቢነግራትም ሳትስማማ ቀርታ ፍለጋው ቀጠለ፡፡

በየኬላው ፍተሻ ሲደረግም ግለሰቧ ዘንዘልማ አካባቢ የገበሬዎች ቤት ካደረች በኋላ የትራንስፖርት ገንዘብ ስላልነበራት በዘንዘልማ ኬላ የሚፈትሹ የአድማ መከላከል ፖሊሶችን ገንዘብ ለመጠየቅ ወደ ኬላው ስትመጣ ቀድሞ የሕፃኑ ፎቶ የደረሳቸው አድማ መከላከል ፖሊሶችና እዛው የነበረ የሕፃኑ አጎት ደርሰው ይዘዋታል፡፡

በዚህ ሂደት ክስ ተመስርቶባት ለምን እንዳደረገችው ስትጠየቅ “ወደ ውጭ ሀገር ለመሄድ ገንዘብ ስላጣሁ” ስትል የእምነት ቃሏን ሰጥታለች።

ፖሊስም የተለያዩ ማስረጃዎችን በማጠናከር ምርመራውን አጣርቶ ለሰሜን ጎጃም ዞን ፍትህ መምሪያ የላከ ሲሆን÷ የባህርዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ትዕግስት አለነ በ13 ዓመት ፅኑ እስራት እንድትቀጣ እንደወሰነባት ከክልሉ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.