በ2016 የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የ8 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል- ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የ8 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ በመደረጉ በተያዘው የ2017 በጀት ዓመትም ኢትዮጵያ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ልታስመዘግብ የምትችልበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል።
ሚኒስትሯ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት የ8 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል ብለዋል።
የሀገር በቀል ኢኮኖሚ አንድ ጀምሮ ለግብርና እና አምራች ኢንዳስትሪ ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት ለጥቅል ሀገራዊ ዕድገት እምርታዊ ለውጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳበረከተም ተናግረዋል።
በዚህም ዋና የኢኮኖሚ ዘርፍ የሚባሉት ግብርና 6 ነጥብ 9 በመቶ፣ ኢንዱስትሪ 9 ነጥብ 2 በመቶ፣ የአገልግሎት ዘርፍ 7 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት ማስመዝገባቸውን አብራርተዋል፡፡
በተመዘገበው ዕድገት፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና የኮንስትራክሽን ዘርፍ ማነቆ የነበረው የሲሚንቶ ችግር መፍትሔ በማግኘቱ የተገኘ ውጤት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ በመደረጉ በ2017 ዓ.ም ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊመዘገብ ይችላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻው በገበያ መር የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር የተሻለ ፍሰት እንዲፈጠር በማድረግ ወጪ ንግድ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በምንዛሬ ተመን ጅምር ውጤት ማሳየታቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የብዝሃ ኢኮኖሚ ልማት ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ዜጎችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ በማድረግ የላቀ ሚና እንዳለውም አንስተዋል።
የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ተዋናዮችን ተወዳዳሪነት በማሳደግ የአልሚ ባለሃብቶችን ተጠቃሚነት ለማሳለጥም ሚናው የገላ ነው ብለዋል፡፡
የግብርና እና የኢንዱስትሪ የገበያ አቅርቦት ፍላጎቶችን በመሙላት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የራሱ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡
በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻው የዜጎችን ተጠቃሚነት ታሳቢ በማድረግ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን መደጎም የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት መዘርጋቱንም አመላክተዋል።