የአፋርና የትግራይ ክልሎችን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር በቁርጠኝነት መስራት ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር እና የትግራይ ክልሎችን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትንና ሰላም ለማጠናከር በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡
በክልሎቹ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እና የጋራ ሰላምን ለማጠናከር በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ የተመራ ቡድን ሰመራ ከተማ ሲገባ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
አቶ አወል አርባ እንደገለፁት፥ የሰላምና ፀጥታ ችግሮችን በመፍታትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ያስፈልጋል።
መረጋጋትን ለመፍጠር የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን በመግለጽ የአፋር ክልል የድርሻውን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፥ በአፋር እና ትግራይ ህዝቦች መካከል የቆየ ወንድማማችነት እና የመደጋገፍ ታሪክ ያላቸው መሆኑን በማንሳት ክልሎች በትብብር ሊያሳኳቸው የሚገቡ በርካታ ተግባራት የሚጠበቅባቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡
የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን እስከ ታችኛዉ መዋቅር ድረስ በማውረድ በግጭቶች የተፈናቀሉ ህዝቦችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው፤ ግንኙነቱን በህዝብ ለህዝብ ደረጃ ለማካሄድ በቀጣይ መድረኮች መፈጠር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
በሁለት ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የህዝብ ለህዝብ ኮንፈረንሶችን ማካሄድና የባህላዊ የግጭት አፈታት ባህሎችን በጋራ በመጠቀም የሚከሰቱ ችግሮችን መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ አመራሮቹ መክረዋል።
በተጨማሪም በክልሎቹ መካከል ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በጋራ የሚሰሩ ስራዎችን ላይ ለመወያየት፣ አልፎ አልፎ በሁለቱም በኩል የሚነሱ ግጭቶችን በፍጥነት ለመፍታትና የተፈናቀሉ ማህበረሰቦችን ወደ ቀያቸዉ ለመመለስ በጋራ በሚሰራባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሄዷል።
የዛሬዉ የመሪዎች ዉይይት ለቀጣይ ግንኙነቶች በር ከፋች መሆኑ መገለጹን ከአፋር ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።