የኢትዮጵያ አየር መንገድ 5 አዳዲስ ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎች ይኖሩኛል አለ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተያዘው በጀት ዓመት አምስት አዳዲስ ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎች እንደሚኖሩት አስታወቀ፡፡
አየር መንገዱ በየዓመቱ መዳረሻዎችን በማስፋትና የአውሮፕላኖችን ቁጥር በመጨመር ዓለም አቀፍ አገልግሎቱን እያጠናከረ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገልጸዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አምስት ተጨማሪ ዓለም አቀፍ መዳራሻዎች ላይ ሥራ መጀመሩን አስታውሰው÷ በ2017 በጀት ዓመትም አምስት አዳዲስ ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎች እንደሚኖሩት ጠቁመዋል፡፡
የበረራ መዳረሻዎች ከሚሆኑት መካከልም አምስተርዳም፣ ሞኖሮቪያ፣ ፖርት ሱዳንና ዳካ ይገኙበታል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አየር መንገዱ እስካሁን ከአውስትራሊያ በስተቀር በሁሉም አህጉሮች የበረራ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አንስተው÷ በሁለት ዓመታት ውስጥ ወደ አውስትራሊያ ለመብረር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ላይ በ147 አውሮፕላኖች 139 ዓለም አቀፍና 22 የሀገር ውስጥ የበረራ መዳረሻዎች እንዳሉትም ተመላክቷል፡፡