የኢትዮጵያና ሕንድ ታሪካዊ ግንኙነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ
አዲስ አበባ፣መስከረም 22፣ 2017(ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያና ሕንድ ታሪካዊ ግንኙነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር አኒል ኩመር ራሂ ተናገሩ።
የሕንድ የነፃነት አባት ሞሃንዳስ ካራምቻንድ ጋንዲ (ማህተማ ጋንዲ) 155ኛ የልደት በዓል ዛሬ በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ተከብሯል።
በመታሰቢያ በዓሉ ላይ በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር የመንግስት ተጠሪዎች፣ የሕንድ ማህበረሰብ አባላትና የሆስፒታሉ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት አምባሳደር አኒል ኩመር ራሂ ሆስፒታሉ የሁለቱ ሀገራት ሁለንተናዊ ትብብር ማሳያ መሆኑን ገልጸው፥ ለሆስፒታሉ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የሕንድ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንትና የንግድ ሥራዎች ጉልህ ተሳትፎ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
የሕንድ መንግስት የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል የሚሰጠውን አገልግሎት ለማጠናከር ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ነው የዘገበው።