ፌዴራል ፖሊስን በአፍሪካ ካሉ ምርጥ አምስት የፖሊስ ተቋማት ውስጥ አንዱ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስን በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ካሉ ምርጥ አምስት የፖሊስ ተቋማት ውስጥ አንዱ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተገለጸ፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዋና መምሪያው ተገኝተው የተቋሙን የሎጂስቲክስ ዝግጁነት ጎብኝተዋል።
በዚህም በአዲስ መልክ የተደራጀው የፖሊስ ጋራዥ የጥገና ማዕከሎች አቅማቸውን በማጎልበትና አሰራራቸውን ወደ ዲጅታል በማሳደግ የከባድና ቀላል ተሸከርካሪ መለዋወጫዎችን በራስ አቅም ማምረት መጀመራቸውን ተመልከተዋል፡፡
በተጨማሪም የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጨምሮ የሌሎች መስሪያ ቤት ተሸከርካሪዎችን ተቀብለው አስተማማኝ የጥገና አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ በጉብኝታቸው ወቅት ተመልክተዋል፡፡
ኮሚሽነር ጀነራሉ በጉብኝቱ ወቅት፤ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ሠራዊት የታጠቃቸውን የሎጂስቲክስ አቅሞችን በቅርበት በመከታተል የጎደሉትን የማሟላት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ይህንኑን ተግባር የበለጠ አጠናክሮ በማስቀጠል በ2022 ዓ.ም የፌዴራል ፖሊስ በአፍሪካ ካሉ ምርጥ አምስት የፖሊስ ተቋማት ውስጥ የሚመደብ፤ ሙያዊ ብቃትን ያረጋገጠ፣ አካታች እና በሕዝብ ታማኝነት ያለው ተቋም ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
አሁን ላይም በርካታ አዳዲስ የአድማ ብተና እና ለግዳጅ አገልግሎት የሚውሉ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን ከውጭ ሀገር በግዥ እንዲገቡ በማድረግ የሠራዊቱን የግዳጅ አፈፃፀም አቅም በሎጂስቲክስ የማጠናክር ስራ መከናወኑን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡