ም/ጠ/ሚ ተመስገን የቢትወደድ ኃ/ጊዮርጊስ ወ/ሚካኤል የቀድሞ መኖሪያ ቤት እድሳትን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል የተዘጋጀውን የቢትወደድ ኃ/ጊዮርጊስ ወ/ሚካኤል የቀድሞ መኖሪያ ቤት እድሳት ጎብኝተዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷ መኖሪያ ቤታቸው የተገነባው ከ119 ዓመታት በፊት መሆኑንም ጠቅሰው÷ቅርስ ሀብታችን ነው፣ ግን ሁለት ነገር ይፈልጋል፣ ማቆየትና ማዘመን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ማቆየት ማለት ለትውልድ እንዲተላለፍ አድርገን መጠገንና ማሣመር ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ማዘመን ደግሞ ይህንና መጪውን ዘመን እንዲያገለግል አድርጎ ማስተካከል ነው ብለዋል፡፡
ቅርስነቱ እንደተጠበቀ ለጉብኝት ማመቻቸት፤ መብራትና ውኃውን ማስተካል፤ የኢንተርኔት መሥመሩን መዘርጋት፤ ለነገ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
አሮጌውን አትንኩት በሚል እስኪፈርስ እያዩ ማጥፋት አይደለም፣ይህ ሕንጻ ለዚህ ምሳሌ ነው፣ ከትናንቱ ማቆየት ያለብን አለ፣ ለዛሬና ለነገ ስንል ደግሞ ማፍረስ ያለብን አለ ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ብልጽግና ትናንትን ከነገ ጋር ማስማማት ነው፣ ትናንት ለነገ ዕንቅፋት ከሆነ ይፈርሳል፣ ትናንት ለነገ ወረት ከሆነ ይጠበቃል፣ ይለማል ብለዋል፡፡
እድሳቱ ዳያስፖራዎች በሀገራቸው ሊኖራቸው የሚገባውን በጎ ተሳትፎ የሚያመለክት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በሰልፍ የሚገነባ ሀገር የለም፣ ሀገር የሚገነባው ወገብ አሥሮ፤ አፈር ነክቶ ሥራ በመሥራት ነው፣ጊዜን፣ ገንዘብን፣ ጉልበትን አፍስሶ ለመጭው ትውልድ የምትመች ሀገር በመሥራት ነው ብለዋል፡፡
ከያኒት ዓለም ፀሐይ ወዳጆም ያደረገችውም ይህንኑ ነው፤ ለዚህ ተምሳሌታዊ ሥራ እናመሰግናለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡