Fana: At a Speed of Life!

በሊባኖስ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የደህንነት ችግር እንዳይደርስ ክትትል እየተደረገ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሊባኖስ የተፈጠረውን ወቅታዊ ሁኔታ ተከትሎ በሀገሪቱ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ደህንነት ላይ ችግር እንዳይደርስ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ዙሪያ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የዋናው መሥሪያ ቤት የሥራ ሃላፊዎችና በሊባኖስ ቤይሩት ቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤት አመራሮች እና ዲፕሎማቶች ጋር በወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ተወያይተዋል።

ውይይቱ በሊባኖስ የተፈጠረው ውጥረት በሀገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች እና ቤይሩት በሚገኘው ቆንስላ ጀኔራል ጽ/ቤት ውስጥ የሚሠሩ ዲፕሎማቶችና ሠራተኞች ደህንነት ላይ ችግር እንዳይደርስ ለማድረግ እየተከናወኑ ባሉ ዝግጅቶች ላይ ያተኮረ እንደነበረ ተገልጿል።

በዚህ ወቅት ሚኒስትር ዴዔታዋ መንግሥት ለዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በሰጠው ቅድሚያ መሠረት ለተፈጠረው ሁኔታ ልዩ ትኩረት በመሥጠት ክትትል እያደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በቀጣይ መንግሥት ለዜጎች በሚደረገው ክትትልና ድጋፍ ዙሪያ በዋናው መስሪያ ቤት፣ በቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤት እንዲሁም በኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ አደረጃጀቶች በኩል መረጃ እንደሚያደርስ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.