Fana: At a Speed of Life!

ኦምኒፖል ኩባንያ ኤል410-ኤንጂ የተሰኘ አውሮፕላን ለኢትዮጵያ ሊያቀርብ ነው

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የቼክ ሪፐብሊክ ኩባንያ የሆነው ኦምኒፖል ለመንገደኞችና ለጭነት ማጓጓዣ የሚውል ኤል410-ኤንጂ የተሰኘ አነስተኛ አውሮፕላን ለኢትዮጵያ ገበያ ሊያቀርብ መሆኑ ተገልጿል፡፡

19 ሰዎችን የመጫን አቅም ያለው እና ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያስገኛል የተባለው ዘመናዊ አውሮፕላን ማስተዋወቂያ መርሐ ግብር ዛሬ ተካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ÷ ኢትዮጵያና ቼክ ሪፐብሊክ የቆየ የትብብር ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረው በአቪዬሽን ዘርፉ ተመሳሳይ ትብብር ለማድረግ የዛሬው መድረክ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል፡፡

የማስተዋወቂያ መድረኩ ክልሎችን በአቪዬሽን ዘርፍ በማስተሳሰር ቱሪዝምን ለማሳለጥና ለማሳደግ እየተደረገ ላለው ጥረት አጋዥ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

ከዚህ በፊት ቼክ ሰራሽ የሆነ ኤል410 ዩቪፒ-ኢ20 ሞዴል አውሮፕላን በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን መመዝገቡን የባለስልጣኑ መረጃ አመልክቷል፡፡

ኤል 410-ኤን ጂ ለመንገደኞች አሊያም ለጭነት አገልግሎት መዋል የሚችልና እጅግ ዘመናዊ መሆኑ ከበፊቱ ልዩ እንደሚያደርገው ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ትንንሽ አውሮፕላኖችንና ሄሊኮፕተሮችን ማሳረፍ የሚያስችሉ ከ21 በላይ ኤርስትሪፖችንና ሂሊፓዶችን በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እያስገነባ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.