ምሁራን የኢሬቻን እሴቶች ለማጎልበት እንዲሠሩ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የዘርፉ ምሁራን የኢሬቻን እሴቶች እና መልካም ገጽታዎች የሚያጎሉ ሥራዎችን እንዲሠሩ የኦሮሚያ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ጥሪ አቀረበ፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳር ጽሕፈት ቤት ያዘጋጀው የ ‘ጉሚ በለል’ የውይይት መድረክ ‘ኢሬቻ ለባህል ሕዳሴያችን’ በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ነው።
የክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ጀሚላ ሲምቢሩ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ በጋራ የሚያከብረው የገዳ ሥርዓት ነፃብራቅ የሆነ የምስጋና እና የአንድነቱ ማሳያ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በስፋት እና በድምቀት እየተከበረ መሆኑን ገልፀው፥ በተለይም የዘርፉ ምሁራን የኢሬቻን እሴቶችና መልካም ገጽታዎች የሚያጎሉ ሥራዎችን እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ ላይ የኢሬቻ ምንነትና ፋይዳ ላይ ያተኮረ መነሻ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡