Fana: At a Speed of Life!

የልብ ህመምን ጨምሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያስከትሉት ጫና አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል – ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያስከትሉት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ዜጎች የአመጋገብ ሥርዓትን በማስተካከል ተጋላጭነታቸውን መቀነስ እንዳለባቸው ጤና ሚኒስቴር አሳሰበ።

የኢትዮጵያ የልብ ማኅበር ከጤና ተቋማት ጋር በመተባበር “ልብን ለተግባር እናውል” በሚል መሪ ሃሳብ ዓለም አቀፉ የልብ ቀን በአዲስ አበባ አክብሯ።

በኢትዮጵያ ለ9ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ25 ጊዜ በተከበረው የልብ ቀን ”የልብና የደም ቧንቧ በሽታ ሁኔታና የሕክምና አገልግሎትን” የሚዳስሱ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር ተደርጎባቸዋል።

በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መካለከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሕይወት ሰለሞን÷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በዜጎች ላይ የሚያስከትሉት ማህበራዊና ኢኮኖሚያ ጫና አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያም ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ ስኳርና ጨው አብዝቶ መጠቀም፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ባህል አለማድረግና ሱስ አምጪ ንጥረ ነገሮች የዜጎችን ታላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭነት ከፍተኛ እንዲሆን እያደረጉት ነው ብለዋል።

የዜጎችን ጤና ለመጠበቅም በቅድመ መከላከል ፖሊሲ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተላላፊ ያልሆኑ የበሽታ ዓይነቶችን ተጋላጭነትን ለመቀነስ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በተለይም የጤና ምርመራ ባህልን ለማሳደግ በቅርበት የጤና ተቋም አገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽነት ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የልብ ማኅበር ፕሬዚዳንት እንዳለ ገብሬ፤÷ የልብ እና የደም ስር ህመሞች በዜጎች ላይ የሚያስከትሉት ማህበራዊና ኢኮኖሚያ ጫና አሳሳቢነት እያደገ መጥቷል ብለዋል።

ህብረሰተሰቡ በኮሊስትሮልና በጉሮሮ ቁስለት የሚከሰትን የልብ ህመም የህክምና ምርመራ በማድረግ ቀድሞ መከላከል እንደሚቻል አስገንዝበዋል።

ተላላፊ ላልሆኑ የበሽታዎች የሚውሉ መድኃኒቶች የአቅርቦት ችግርን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የልብ ሕክምና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ እና አገልግሎቱም ያልተስፋፋ በመሆኑ ዜጎች የቅድመ መከላከልና የምርመራ ባህል ማሳደግ ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸውም ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.