አቶ ኦርዲን በድሪ በክልሉ የለማውን የማሽላ ኢንሼቲቭ ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች በክልሉ በኩታ ገጠም የለማውን የማሽላ ኢንሼቲቭ ጎበኙ፡፡
“መልካም” የተባለውና ከፍተኛ ምርት የሚሰጠውን ማሽላ በክልሉ የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ነስረዲን አህመድ እንደገለፁት÷ በክልሉ በ800 ሔክታር መሬት ላይ “መልካም” የተሰኘ ምርጥ የማሽላ ዝርያ በኩታ ገጠም እየለማ ነው።
የማሽላ ዝርያው የዝናብ እጥረትንና በሽታን በመቋቋም በሔክታር እስከ 43 ኩንታል ምርት መስጠት ይችላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ይህም ቀደም ሲል ከነበረው ከእጥፍ በላይ ብልጫ ምርታማነት እንዳለው ገልፀዋል።
“መልካም” የተባለውን የማሽላ ዝርያ በክልሉ አሁን ካለው ከ800 ሔክታር ወደ 6 ሺህ 337 ሔክታር መሬት ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
የዝርያው መስፋፋት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየተከናወነ የሚገኘውን ስራ ስኬታማ ማድረግ እንደሚያስችልም አመላክተዋል፡፡