ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለልማት ተነሺ ነዎሪዎች የተገነቡ ቤቶችን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ)የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በኮሪደር ልማት እና ለመልሶ ማልማት ተነሺ ለሆኑ ነዋሪዎች የተገነቡ ምትክ ቤቶችን ጎብኝተዋል፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ÷ ለልማት ተነሺዎች የተገነቡት የመኖሪያ ቤቶች ውሃ፣ መብራት፣ መጸዳጃ እና ማብሰያ ቦታ የተገነባላቸው መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ቤቶቹ ለስራ እድል የሚሆኑ የመስሪያ ሼዶች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ የንግድ ሱቆች እንዲሁም ትምህርት ቤቶች ያላቸው የመኖሪያ መንደሮች መሆናቸውን ጠቅሰው ፋርማሲዎች እና የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በተጨማሪ ም ከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ተመሳሳይ የመኖሪያ መንደሮችን ዝግጁ በማድረግ ከመኖሪያ አካባቢያቸው ለሚነሱ ነዋሪዎች እያስተላለፈ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡
በመልሶ ማልማቱ ነዋሪዎች ማህበራዊ መሰረታቸው ሳይበጠስ በጋራ አንድ አካባቢ እንዲገቡ መደረጉንም ነው የገለፁት፡፡