ድንበር ተሻጋሪ የዜጎች ፍልሰትን የተመለከተ ቀጣናዊ አውደ ጥናት በቀጣዩ ሳምንት በኢትዮጵያ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ)ድንበር ተሻጋሪ የዜጎች እንቅስቃሴና ፍልሰትን የተመለከተ ቀጣናዊ አውደ ጥናት በቀጣዩ ሳምንት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) አስታወቀ።
መስከረም 22 እና 23 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄደው አውደ ጥናቱ የኢጋድ አባል አገራት ድንበር ዘለል የዜጎች እንቅሰቃሴና ፍልሰት ላይ ያላቸውን ተሞክሮ በመለዋወጥ ቀጣናዊ ትስስር እና ትብብርን ማጠናከር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
ኢጋድ በቀጣናዊ ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ላይ የወሰዳቸው እርምጃዎች ያስገኛቸው ውጤቶች እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ያሉ እድሎችና ፈተናዎች ምክክር ዙሪያ እንደሚደረግ ተመላክቷል።
በድንበር አካባቢ ያሉ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች እና የተቀባይ አገራት ዜጎችን ኑሮ ማሻሻል በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ውይይት እንደሚካሄድ ተመላክቷል፡፡
ቀጣናዊ አውደ ጥናቱ የኢጋድ የፍልሰት መርሃ ግብር አካል መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡