ኢንስቲትዩቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አቅም የተላበሱ የደህንት ካሜራዎችን ለሶማሌ ክልል አበረከተ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የሰው ሰራሽ አስተውሎት አቅም የተላበሱ የተለያዩ የደህንት ካሜራዎችን ለሶማሌ ክልል በድጋፍ አበረከተ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በርክክቡ ወቅት፤ ድጋፉ ኢንስቲትዩቱ የስማርት ሲቲ ፕሮጀክት በመንደፍ ከተሞችን ለነዋሪዎችና ለጎብኝዎች ምቹ ለማድረግ የሚሰራው ተግባር አካል መሆኑን ተናግረዋል።
ካሜራዎቹ 70 ሚሊየን ብር ግምታዊ ዋጋ እንዳላቸው ገልጸው፤ ድጋፉ ኢትዮጵያ ለነደፈችው የዲጅታል ስትራቴጂ ተግባራዊነት ሚናው ጉልህ መሆኑን ማንሳታቸውን የኢንስቲትዩቱ መረጃ አመላክቷል።
የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሀሰን ሞጎ በበኩላቸው ድጋፉ የሰላም እና ፀጥታ ስራውን በቴክኖሎጂ በማገዝ ወንጀል በመከላከል ረገድ አስተማማኝ አቅም ለማዳበር ያግዛል ብለዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ምርምር እና ልማት ስራ ዕድገትን ለማፋጠን እንደሚያስችል ጠቅሰው፤ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።