የመስቀል ደመራ በዓል በተለያዩ ከተሞች እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስቀል ደመራ በዓል በተለያዩ ከተሞች በድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡
በዓሉ በጅማ ከተማ በደማቅ እየተከበረ ሲሆን የእምነቱ ተከታዮች እና በከተማዋ ከሚገኙ 17 ደብራት የተውጣጡ የተለያዩ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች እንዲሁም አባቶች በዓሉን በዝማሬና በተለያዩ ስነ ስርዓቶች እያከበሩ ይገኛሉ።
የመስቀል በዓል ስነ ስርዓቱን የፈለገሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ያዘጋጀ ሲሆን፤ የጅማ፣ የም እና ሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁ አቡነ እስጢፋኖስ ቡራኬን በመስጠት በዓሉን አስጀምረዉታል።
በተመሳሳይ በዓሉ በነቀምቴ ከተማ በመከበር ላይ ሲሆን የእምነቱ ተከታዮች እና በከተማዋ ከሚገኙ 10 አድባራት የተውጣጡ የተለያዩ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣ አባቶች እንዲሁም የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በበዓሉ ታድመዋል፡፡
የመስቀል ደመራ በዓል በሻሸመኔ ከተማም የምዕራብ አርሲና ቦረና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ በተገኙበት በሀይማኖታዊ ስነ-ስርዓቱ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
እንዲሁም በደብረብርሃን ከተማ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ካህናት አባቶች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያን እንዲሁም ህዝበ ክርስቲያኑ በተገኙበት በአፄ ዘርዐ ያዕቆብ አደባባይ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በዓሉ በወላይታ ሶዶ ከተማም የተለያዩ የበዓሉ ታዳሚዎች በተገኙበት በድምቀት በመከበር ላይ ነው፡፡
በተመሳሳይ የመስቀል ደመራ በዓል በሀረር ከተማ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በተለያዩ ሀይማኖታዊ ስነስርዓቶች በድምቀት መከበሩን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
መረጃውን ያደረሱን ከየከተሞቹ የተገኙ ሪፖርተሮቻችን ናቸው፡፡