መስቀሉ ባስተማረው መሰረት ችግሮችን በሰላም በእኩልነትና በፍቅር መፍታት ይገባል – ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2017(ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን እየተፈታተኑ ያሉ ችግሮችን መስቀሉ ባስተማረው መሰረት በሰላም በእኩልነትና በፍቅር መፍታት እንደሚገባ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ገለጹ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ኃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በመስቀል አደባባይ በደማቅ ሥነ ሥርዓት እየተከበረ ይገኛል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በመስቀል አደባባይ የሚከበረውን የደመራ በዓል ባርከዋል፡፡
በዚህ ወቅትም ባስተላለፉት መልዕክት ፥ መስቀል ከቁሳዊ ይልቅ መንፈሳዊ ሀይል እንደሚበልጥ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመስቀል ደመራ በዓል የሚከበረው ኃይለ እግዚአብሔርን ለማሰብና የመስቀሉ ሀያልነትና አሸናፊነት በሀቅና ሰላም ላይ የተመሰረተ መሆኑን ለማሳየት ነው ብለዋል፡፡
በዓለም ላይ እርስ በእርስ አለመተማመን እንዲፈጠር ያደረገ በመስቀሉ ላይ የሚተላለፈው መልዕክት ገቢራዊ ባለመደረጉ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያን እየተፈታተኑ ያሉ ችግሮችን መስቀሉ ባስተማረው መሰረት በሰላም በእኩልነትና በፍቅር መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ሰርተው እንዲለወጡ መንግስትና ኢትዮጵያውያን ለዘላቂ ሰላምና አንድነት አበክረው እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡