አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከግሪክና ሴራሊዮን አቻዎቻቸው ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ኢትዮጵያ ከግሪክ እና ሴራሊዮን ጋር ያላትን ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ዙሪያ ከሁለቱ ሀገራት አቻዎቻቸው ጋር ተወያይተዋል።
ሚኒስትሩ ከግሪኩ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊኦርጎስ ጀርፐትራይተስ ጋር ባደረጉት ውይይት ግሪክ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት አባል ሆና በመመረጧ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።
አምባሳደር ታዬ ወቅታዊውን የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ በሚመለከት ለሚኒስትሩ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ኢትዮጵያ የምታደርገውን ፀረ-ሽብር ዘመቻ አጠናክራ ለመቀጠል ያላትን ቁርጠኝነት ገልፀዋል።
በተመሳሳይ አምባሳደር ታዬ ከሴራሊዮን ውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ጢሞቲ ካባ ጋር በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና ደኀንነት ዙሪያ መክረዋል።
ሚኒስትሩ በሶማሊያ ከአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ሰላም ማስከበር ተልዕኮ (አትሚስ) በኋላ የሚኖረው የኃይል ሥምሪት ጊዜ ተወስዶ በጥንቃቄ መከናወን እንዳለበት መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።