የመስቀል ደመራ በዓል ሲከበር ሰላምን በማጽናትና አብሮነትን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስቀል ደመራ በዓልን ስናከብር ከምንም በላይ ሠላማችንን በማጽናትና አብሮነታችንን በማጠናከር ሊሆን ይገባል ሲል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገለጸ፡፡
የክልሉ መንግስት ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ2017 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በሠላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቱን ገልጿል፡፡
የክልሉ መንግስት የመስቀል ደመራ በዓልን ስናከብር ከምንም በላይ ሠላማችንን በማጽናት፣ አብሮነታችንን በማጠናከር እንዲሁም የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በመደገፍ ሊሆን ይገባል ሲል ጥሪ ማቅረቡን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩት በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የመስቀል ደመራ በዓል መስቀል የብርሃንና የድኅነት ምልክት መሆኑን በማሰብ በአደባባይ እንደሚከበር አንስቷል።
መስቀል የጠላት ማሸነፊያ ምልክት ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑ፣ ሁላችንም ከድህነት ጀምሮ ጠላቶቻችንን የምናሸንፍበት ምስጢር የሆነውን ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ማጠናከር ይጠበቅብናል ሲልም የክልሉ መንግሰት መልዕክት አስተላልፏል፡፡