እንደ ደመራው ተደምረን ልዩነቶችን በማስወገድ ለአንዲት ኢትዮጵያ መቆም ይገባናል – ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)
አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) እንደ ደመራው ተደምረን ልዩነቶችን በማስወገድ ለአንዲት ኢትዮጵያ መቆም ይገባናል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ የመስቀል በዓል አንድነት፣ አብሮነትና መደመር የሃያልነት፣ የመድመቅና የመጉላት መሰረት መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።
የብዙ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ስብስብ የሆነችው ኢትዮጵያ የደመራ ምሳሌ ናት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ እኛ ኢትዮጵያውያንም ከየአቅጣጫው ተሰባስበን መከራን፣ ጦርነትንና ግጭትን ተጋፍጠን ሀገርን አጽንተናል ሲሉም ተናግረዋል።
ችግሮችና መከራዎችን በመቋቋም በጽናትና በትዕግስት በማለፍ እንደ ደመራው አንድ በመሆን ኢትዮጵያ ወደሚጨበጥ ብርሃን እንድታመራ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ መሰብሰባችን ታላቅ ሀገራዊ ብርሃንን እንድናበራ አይነተኛ ምሳሌያችን ነው ብለዋል።
እንደ ደመራው ተደምረን ልዩነቶችን በማስወገድ ለአንዲት ኢትዮጵያ መቆም ይገባናል ሲሉ አስገንዝበዋል።
የመስቀል በዓል የአዳዲስ እሳቤዎች የሚነገሩበት ከጨለማ ወደ ብርሃን የምንሸጋገርበት አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበት የጠብ ግድግዳ የሚፈርስበት ሰላም የሚሰበክበት ብሩህ ተስፋ የሚሰነቅበት ጊዜ ነው ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።