የፓኪስታን ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስት ማድረግ እንፈልጋለን አሉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፓኪስታን ባለሀብቶች ድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣናን ጨምሮ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚፈልጉ ገለጹ፡፡
በኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሽፈራው ሰለሞን ከፓኪስታን ባለሃብቶች ጋር ተወያይተዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ኮርፖሬሽኑ በሚያሥተዳድራቸው 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና ያሉ መሠረተ-ልማቶችን እና የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን ዋና ሥራ አስኪጁ አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ያለው ወጣትና የተማረ የሰው ኃይል፣ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ እንዲሁም በመንግሥት በኩል የተሠጠው ትኩረት ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ኢንቨስት ለማድረግ ትክክለኛ ቦታ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የፓኪስታን ባለሃብቶች በበኩላቸው÷ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በአልሙኒዬም፣ ብረታ ብረትና የወረቀት ፓኬጂንግ ዘርፎች ኢንቨስት ማድረግ እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል፡፡
ለዚህም የቅድመ ኢንቨስመንት ጉብኝት እያደረግን ነው ማለታቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡