በእስራኤልና ሂዝቦላህ መካካል የሚካሄደውን ጦርነት የማስቆም አቅም ያላት አሜሪካ ብቻ ናት ስትል ሊባኖስ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በእስራዔልና ሂዝቦላህ መካካል የሚካሄደውን ጦርነት የማስቆም አቅም ያላት አሜሪካ ብቻ እንደሆነች የችግሩ ሰለባ የሆነችው ሊባኖስ አስታወቀች።
የሁለቱ ወገኖች ጦርነት መነሻ አጋርነቱን ለሃማስ ለማሳየት ሚሳዔሎችን ወደ እስራዔል ማስወንጨፍ በጀመረው ሂዝቦላህ ላይ እስራዔል አመራሮች ላይ የታለመ እርምጃ መውሰዷ እንደሆነ ተነግሯል።
እስራኤል ለሂዝቦላህ ጥቃት በሰጠችው ምላሽና በወሰደችው የአየር ጥቃት የሂዝቦላክ ከፍተኛ አዛዥ የሆነውን ኢብራሂም አቂልን ገድላለች።
ይህንን ተከትሎ በእስራዔልና በሂዝቦላህ መካከል ያለው ጦርነት እየተባባሰ የመጣ ሲሆን እስራኤል የሂዝቦላህ ኢላማዎች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ስትፈጽም፤ ሂዝቦላህም በምላሹ በእስራኤል ግዛት የሮኬት ጥቃት እየፈፀመ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጦርነቱ እንዲቆም ጥሪ ቢያቀርቡም ሊባኖስ ጥሪው ጠንካራ እንዳልሆነ ገልጻለች።
የሊባኖስ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አብደላህ ቦው ሃቢብ አሜሪካ ጦርነቱ እንዲቆም ጠንከር ያለ አቋም ማንጸባረቅ እንዳለባት ተናግረዋል።
ጦርነቱን የማስቆም አቅም ያላት አሜሪካ ብቻ መሆኗን መናገራቸውን የዘገበው ሬውተርስ ነው።
የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመው የአየር ጥቃት በርካታ የሂዝቦላህ ኢላማዎችን ያወደመ ሲሆን፤ ከ558 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ አካባቢያቸውን ለቀው መውጣታቸው መገለጹ ይታወቃል።
ሂዝቦላህ በበኩሉ÷ የእስራኤል ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ የሮኬት ጥቃት እየፈጸመ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።