ክልሎች የመስቀል ደመራ በዓልን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስቀል ደመራ በዓልን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የተለያዩ ክልሎች አስታውቀዋል፡፡
የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ረምዚ ሱልጣን እንዳሉት÷ በዓሉን በድምቀት ለማክበር ኮሚሽኑ ከሀገር መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ፣ ከጸጥታ አካላት እና ከክልሉ ሕዝብ ጋር በቅንጅት እየሠራ ነው፡፡
በተመሳሳይ የመስቀል ደመራ በዓል ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ይዘቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውን የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኡጉላ ኡጁሉ አስታውቀዋል፡፡
እንዲሁም የመስቀል ደመራ እና የግሸን ደብረ ከርቤ በዓላትን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ክፍል ኃላፊ ምክትል ኮማንደር መሳፍንት እሸቴ ተናግረዋል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመስቀል ደመራ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር ተከብሮ እንዲውል በቂ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍስሃ ጋረደው አስታውቀዋል፡፡