ፓርኩ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን ለማምረት ማቀዱን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በበጀት ዓመቱ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ተኪ ምርቶችን ለሀገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ፓርኩ እቅዱን ለማሳካትና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ይበልጥ ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።
የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጉልላት አበበ እንደገለፁት÷ ፓርኩ ውስጥ ከገቡት 13 ኩባንያዎች መካከል 11 የሚሆኑት ወደ ምርት ገብተዋል።
ቀሪዎቹን ኩባንያዎች በሁለት ወራት ውስጥ ወደ ምርት ለማስገባት ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ፓርኩ ለውጭ ገበያ ከሚያቀርበው ምርት በተጨማሪ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው ውስጥ የራሱን ድርሻ ለመጫወት አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን ነው የገለጹት።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው በፓርኩ ውስጥ ወደ ማምረት የገቡ ባለሃብቶችን ከማነቃቃት ባለፈ ተጨማሪ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ምቹ አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል።
የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ 9 ሺህ ለሚሆኑት ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ሥራ አስኪያጁ ለኢዜአ ገልጸዋል።