ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት የደረሰችባቸው የኢኮኖሚ ትብብር ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንደሚደረጉ አረጋገጠች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት የተደረሰባቸው የኢኮኖሚ ትብብር ፕሮጀክቶች እንዲሁም ከቀረጥና ታሪፍ ነፃ የገበያ ዕድሎቸ ትኩረት ተሠጥቷቸው ተግባራዊ እንደሚደረጉ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዩ አስታወቁ፡፡
በኒውዮርክ እየተካሄደ ከሚገኘው 79ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሤ ከቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዩ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ አምባሳደር ታዬ፥ በቅርቡ በቻይና በተካሄደው 4ኛው የቻይና አፍሪካ መድረክ (ፎካክ) የመሪዎች ጉባዔ ወቅት ኢትዮጵያና ቻይና ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩ በርካታ ስምምነቶች መፈራረማቸው ለግንኙነታቸው የሚሠጡት የላቀ ትኩረት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ የፎካክ ጉባዔ የአፍሪካ ብሎም የኢትዮ-ቻይና ስትራቴጂካዊ አጋርነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ መሆኑን አውስተዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር የምትጫወተውን ቁልፍ ሚና ያደነቁት ሚኒስትር ዋንግ ዩ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት ”የምንጊዜም ስትራቴጂክ አጋርነት” መሆኑ በቀጣይ በርካታ ሥራዎችን በጋራ ለመስራት መሠረት መጣሉን ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቻይና ጉብኝት ወቅት ስምምነት የተደረሰባቸው የኢኮኖሚ ትብብር ፕሮጀክቶች እንዲሁም ከቀረጥና ታሪፍ ነፃ የገበያ ዕድሎቸ ትኩረት ተሠጥቷቸው ተግባራዊ እንደሚደረጉ አረጋግጠዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሤ በዚህ ወቅት የአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያም ገለጻ ሠጥተዋል።
ሁለቱ ሚኒስትሮች ኢትዮጵያና ቻይና ብሪክስን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በጋራ መስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሃሳብ መለዋወጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።