በሶማሊያ በውጭ ሃይላት የሚደረግ የጦር መሣሪያ አቅርቦት ሀገሪቷ በአሸባሪዎች እጅ ላይ እንድትወድቅ በር ይከፍታል – አምባሳደር ታዬ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሊያ ባልተረጋጋ የደህንነት ሁኔታ ውስጥ በውጭ ሃይላት የሚደረግ የጦር መሣሪያ አቅርቦት በመጨረሻ ሀገሪቷ አሸባሪዎች እጅ ላይ እንድትወድቅ በር ሊከፍት ይችላል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሤ ተናገሩ፡፡
አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሤ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ግንባታ እና ፖለቲካ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሐፊ ሮዝማሪ ዲካርሎ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም አምባሳደር ታዬ በ ተመድ ጥላ ሥራ የሚገኙ የተለያዩ ኤጀንሲዎች ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ የሥራ ግንኙነት ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን በማድነቅ ቀጣይነት ያላቸው መደበኛ ምክክሮችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡
በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ገለጻ ያደረጉት አምባሳደሩ÷ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ እና ኢትዮጵያ ለሱዳን ቀውስ መፍትሔው ፖለቲካዊ ነው ሚል አቋም እንዳላት አስገንዝበዋል።
ወቅታዊውን የሶማሊያ ጉዳይ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ÷ኢትዮጵያ ሽብርተኞችን ለመዋጋት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
በሶማሊያ ድህረ የአፍሪካ ህብረት ሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ (አትሚስ) የሚኖረው የኃይል ስምሪት ተገቢውን ጊዜ ወስዶ የተልዕኮዎን የኃላፊነትን ፣ መጠን፣ የፋይናንስ ምንጭ እና ቅንጅት በአግባቡ መሠራት እንዳለበት አስረድተዋል።
ሶማሊያ ባልተረጋጋ የደህንነት ሁኔታ ውስጥ በውጭ ኃይላት የሚደረግላት የጦር መሣሪያ አቅርቦት አሸባሪዎች እጅ ላይ ሊወደቅ እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልፀዋል።
ሮዝማሪ ዲካርሎ በበኩላቸው ÷በቀጣናው እና ከቀጣናው ባሻገርም ተመድ ከኢትዮጵያ ጋር በሰላም ግንባታ ዙሪያ የሚያደርገውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።