ጥናት በማድረግ የዘረፋ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 14 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በግለሰቦች ላይ ጥናት በማድረግ የዘረፋ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በቦሌ ክ/ከተማ ልዩ ልዩ ስፍራዎች ላይ ትኩረት አድርገው የቅሚያና የዘረፋ ወንጀል ሊፈፀምባቸው የሚችሉ ግለሰቦችን አስቀድሞ በማጥናት ወንጀሉን ሲፈፅሙ እንደነበር ተመላክቷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ መሰረት ኪዳኔ፣ ሐብቶም ሐይሉ፣ ኬቨን አማኑኤል፣ አብርሀም አፅባ፣ሙሉጌታ መክት፣ አብርሀም ማናሰበ፣ ሁሴን ዳውድ፣ አማኑኤል ሐይሌ፣ እዮብ አለማየሁ፣በድሉ ደጉ፣ ምስኪ አድማሱ እና ሰለሞን ታደሰ የተባሉ በአጠቃላይ 14 ግለሰቦች ናቸው፡፡
ፖሊስ ወንጀል ፈፃሚዎቹን ለይቶ በቁጥጥር ስር ለማዋል በክትትል ላይ እንዳለ በፖሊስ ሲፈለግ የነበረው አንድ ተጠርጣሪ ከአንዲት ግለሰብ 33ሺህ ብር የሚያወጣ ሞባይል ስልክ ቀምቶ ለማምለጥ ሲሞክር መያዙ ተጠቁሟል፡፡
በተጠርጣሪው ላይ በተከናወነ ምርመራ ከዚህ ቀደም በክ/ከተማው ወረዳ 3 ቦሌ መድሃኔዓለምና በወረዳ 2 ቦሌ ፍሬንድሺፕ፣ደሳለኝ ሆቴል እና ሳፋሪ አዲስ አካባቢ በሌሎች ግለሰቦች ላይ ተመሳሳይ ወንጀል መፈፀሙ ተረጋግጧል፡፡
በሌላ የወንጀል ድርጊት ትኩረታቸውን በቤት መስበር ስርቆት ላይ ያደረጉ ወንጀል ፈፃሚዎችን ለመያዝ በተደረገ ክትትል ቢኒያም አለማየሁ እና ይድነቃቸው ጋረደው የተባሉት ተጠርጣሪዎች መያዛቸው ተገልጿል፡፡
ወንጀል ፈፃሚዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተደረገ ክትትል በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ተመሳሳይ ቁልፍ በመጠቀም የአንድን ግለሰብ መኖሪያ ቤት ከፍተው በመግባት 1ሺህ 688 የአሜሪካ ዶላር፣ 61 የእንግሊዝ ፓውንድ እና 17 ሺህ 250 ብር ሰርቀው ሲወጡ እጅ ከፍንጅ እንደተያዙ ተጠቅሷል፡፡
ግለሰቦቹ በፈፀሟቸው ወንጀሎች በአጠቃላይ 4 መዝገቦች ተደራጅቶ እና ክስ ተመስርቶ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ እንደሚገኝ እና የቤት ሰብሮ ስርቆት በፈፀሙት ላይ ምርመራው ተጠናክሮ መቀጠሉን የፖሊስ መረጃ አመልክቷል፡፡
ወንጀል ፈፃሚዎቹ ወንጀሉን የሚፈፅሙት በቦሌ ክ/ከተማ ልዩ ልዩ ስፍራዎች በመንቀሳቀስ ግለሰቦችንና መኖሪያ ቤቶችን አስቀድመው በማጥናት ሲሆን÷በሰው አካል ላይ ጉዳት በማድረስ ጭምር ወንጀሉን ሲፈፅሙ መቆየታቸው ተገልጿል፡፡