Fana: At a Speed of Life!

የመስቀል ደመራ በዓል ኃይማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስቀል ደመራ በዓል ኃይማኖታዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች ጋር ውይይት አድርጓል::

የቢሮው ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በውይይቱ ወቅት÷ የመስቀል ደመራ በዓል ኃይማኖታዊ ትውፊቱን እና ሰላማችንን በሚገልፅ መልኩ እንዲከበር ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል ብለዋል።

የከተማዋ ድምቀት የሆነው የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርገን አጠናቅቀናል ሲሉም ተናግረዋል::

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው÷ በዓሉ ምንም የጸጥታ ስጋት ሳይኖር እንዲከበር ፖሊስ በአዲስ አበባ ካሉ አድባራት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ፖሊስ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁንም መግለጻቸውን ከአዲስ አበባ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ስራ አስኪያጅ እና የባህርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም÷ የደመራ በዓል በታቀደው መንገድ ሰላማችንን እና አንድነታችንን በሚገልፅ መልኩ ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ምዕመኑ ከጸጥታ አካላት ጋር በትብብር እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.