Fana: At a Speed of Life!

በሱዳን ያለው ቀውስ በነዳጅ አቅርቦቷ ላይ ተጽዕኖ ማስከተሉን ደቡብ ሱዳን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሱዳን ያለው ቀውስ በትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት መፍጠሩ በነዳጅ አቅርቦቷ ላይ ተጽዕኖ ማስከተሉን ደቡብ ሱዳን ገለጸች።

በነዳጅ ማስተላለፊያዎች ባሉባቸው አካባቢዎች በመሃመድ ሀምዳን ዳጋሎ (ሄምቲ) የሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ታጣቂዎች መኖራቸው ችግሩን እንዳባባሰው ተነግሯል።

ይህንን ችግር ለመፍታት በጁባ የመከሩት የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት እና ከሱዳኑ የሉዓላዊ ሽግግር ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጄኔራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን በሀገራቱ መካከል የተዘረጋው የነዳጅ ማስተላልፊያ መስመር በጦርነቱ ጉዳት ማስተናገዱ ገልጸዋል።

የነዳጅ ማስተላለፊያዎቹን ለመጠገን አመቺ ሁኔታ አለመኖሩ ችግሩን እንዳባባሰውም ተነግሯል።

በሱዳን ያለው ጦርነት ችግሩን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ ቢያደርገውም የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሩን ለመጠገን እንዲሁም እንቅፋቶችን በማስወገድ መስመሩ ዳግም ስራ እንዲጀምር ለማስቻል ከስምምነት ደርሰዋል።

ለዚህም ችግሩን ለመፍታት ከሁለቱም ሀገሮች የነዳጅ ሚኒስቴር የተውጣጡ አባላት ያሉት የጋራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ወስነዋል።

የቀድሞ የሱዳን የነዳጅ ሚኒስትር ሃሚድ ሱሌማን፤ ሱዳን ውስጥ እየተፋለሙ ባሉ ሃይሎች መካከል ያለው ቀውስ መፍትሄ ካላገኘና ሰላም ካልሰፈነ በስተቀር የነዳጅ ማስተላፊያ መስመሩን ዳግም ወደ ስራ ማስገባት እንደማይቻል አስገንዝበዋል።

አካባቢው የጦርነት ቀጠና መሆኑ እንዲሁም መስመሩ በፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መሆን ለስራው አደጋች መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ወቀሳ የቀረበበት የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ በበኩሉ በነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሩ ላይ ጉዳት አለማድረሱን ገልጾ፤ የሱዳን ጦርን ተጠያቂ ማድረጉን ራዲዮ ዳባንጋን ጠቅሶ ኦልአፍሪካ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.