የኢራን አብዮታዊ ዘብ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛዎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ አገደ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢራን አብዮታዊ ዘብ ፔጀር እና ዎኪ ቶኪ የተባሉት የአሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች በአባላቱ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማገዱ ተገለፀ፡፡
ክልከላው በግንኙነት መሳሪዎች ፍንዳታ ምክንያት በርካታ የሂዝቦላህ ታጣቂ ቡድን አባላትና አመራሮች ለሞት እና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን ተከትሎ መሆኑ ተነግሯል።
የኢራን ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣናት ለሬውተርስ እንደተናገሩት÷ በሀገር ውስጥ የተመረቱ እንዲሁም የቻይና እና ሩሲያ ሰራሽ የግንኙነት መሳሪያዎች በኢራን አብዮታዊ ዘብ ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር፡፡
ለእስራኤል የሚሰሩ ሰዎች ወደ ኢራን ሰርገው ሊገቡ እንደሚችሉ እና ይህም የኢራን የደህንነት ስጋት በመሆኑ የመገናኛ መሳሪያዎቹን የመፈትሽ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም የአብዮታዊ ዘቡን አመራሮች መሰረት ያደረገ ፍተሻ እየተከናወነ ጠቅሰው÷ አባላቱ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ያላቸውን የባንክ ሂሳብ፣ የጉዞ ታሪክ እና የቤተሰቦቻቸውን ሁኔታ የመመርመር ስራ እየተከወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል በሂዝቦላህ አባላት በብዛት ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩት የፔጀር እና ወኪ ቶኪ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች በተመሳሳይ ሰዓት በሊባኖስ መፈንዳታቸውን ተከትሎ 12 የሂዝቦላህ አባላትን ጨምሮ 39 ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡