በምግብ እራስን የመቻል ግብን ማሳካት እንደሚቻል የተጀመሩ ሥራዎች ማሳያ ናቸው – የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) እንደ ሀገር በምግብ እራስን ለመቻል የተያዘውን ግብ ማሳካት እንደሚቻል የተጀመሩ ሥራዎች ማሳያ ናቸው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ፡፡
በአዳማ ከተማ እየተሰጠ የሚገኘው የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና እንደቀጠለ ነው።
ክፍተኛ አመራሮቹ ከስልጠናው ጎን ለጎን በዛሬው ዕለት በአዳማ ከተማ ዙሪያ እየተሰሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም÷ የፓፓያ፣ የአቮካዶ ፣ የዶሮ እርባታ፣ የእንስሳት ተዋጽኦ እና ሌሎች በግብርናው ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
የሚሰጠው ስልጠና በተግባር መሬት ላይ የወረደ መሆኑን ከጉብኝታቸው መገንዘብ መቻላቸውን አመራሮቹ ተናግረዋል።
ፓርቲው የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የያዘውን ግብ እውን ለማድረግ አበክሮ እየሰራ እደሚገኝ በጉብኝቱ ማረጋገጥ መቻላቸውን ጠቅሰዋል።
በየአከባቢያቸው የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመው÷ ተግባራቱን ይበልጥ ለማጠናከር ከጉብኝታቸው ተሞክሮ መውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡
በታሪኩ ለገሰ