የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ “ዮዮ ጊፋታ” በዓል ተከበረ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ “ዮዮ ጊፋታ” በዓል በወላይታ ሶዶ ስታዲየም በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡
ጊፋታ የወላይታ ሕዝብ አሮጌውን ዘመን ሸኝቶ አዲሱን የሚቀበልበትና ተራርቀው የቆዩ ዘመድ አዝማድ ተገናኝተው በፍቅር የሚያከብሩት በዓል መሆኑ ተገልጿል፡፡
የኢፌዲሪ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ተወካይ አቶ ጌታቸው ኤርቤራ÷ የጊፋታ በዓልን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጰጥሮስ ወ/ማርያም በበኩላቸው÷ የጊፋታ በዓል የአብሮነትና መቻቻል በዓል እንደሆነ አውስተዋል።
የጊፋታ በዓል የራሱ የሆነ የጊዜ አቆጣጠር እንዳለው ጠቁመው÷በዓሉ የይቅርታ፣ የእርቀ እና የሰላም ምልክት ነው ብለዋል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ተወካይ አቶ አካሉ አስፋው÷ሰላም፣ እርቅ ፣ አንድነት እና ሌሎች እሴቶች የጊፋታ መገለጫች በመሆናቸው ማሳደግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በአከባበር ሥነ-ሥርቱ የፈረስ ጉግስ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት፣ የጊፋታ መለያ የሆነው የሌኬ ጫዎታ እና ሌሎች ተግባራት ተከናውኗል።
በማቴዎስ ፈለቀ