Fana: At a Speed of Life!

“ሊባኖስ ሌላኛዋ ጋዛ እንድትሆን አንፈቅድም”- ተመድ

አዲስ አበበ፣ መስከረም 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) “ሊባኖስ ሌላኛዋ ጋዛ እንድትሆን መፍቅድ የለብንም” ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሳሰቡ፡፡

ዋና ጸሐፊው በእስራኤል እና ሂዝቦላህ መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት ሊቆም እንደሚገባ ከዓረብ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

የጋዛው ጦርነት ከተከሰተ ጀምሮ በርካቶች ካሰቡት በላይ ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን አስታውሰው÷ ጦርነቶችን ማስቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ሃማስ በደቡባዊ እስራኤል የፈፀመውን ጥቃት ያወገዙት ዋና ጸሐፊው÷ በእስራኤል የአፀፋ ጥቃትም የፍልስጤም ሕዝብ ሊቀጣ እንደማይገባው ገልጸዋል፡፡

ተመድ የተኩስ አቁም እንዲደረግ በተዳጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርብም በተፋላሚዎቹ ዘንድ ውድቅ መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡

አሁንም በርካቶችን እየቀጠፈና እያፈናቀለ ያለው የእስራኤል እና ሂዝቦላህ ጦርነት መባባስ ተቋማቸውን እንደሚያሳስበው አስረድተዋል፡፡

ጦርነቱ በአፀፋ ጥቃት ምክንያት እየተባባሰ ሊባኖስ ሌላኛዋ ጋዛ እንድትሆን መፍቅድ የለብንም፤ በጋዛ እና በሊባኖስ የሚደረጉ ጦርነቶችን በማስቆም የንፁሃን ዜጎችን እልቂት መቀነስ ይገባናል ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

ሰሞኑን የሂዝቦላህ ታጣቂዎች እንሚጠቀሟቸው የተነገረላቸው የመገናኛ መሣሪያዎች ፈንድተው ከ12 በላይ ሰዎች ሰዎች ሲሞቱ÷ ትናንት ምሽት እስራኤል በቤይሩት በፈፀመችው ጥቃት ከ37 የሚልቁ ሰዎች ሕይወት ማለፉን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስትር አስታውቀዋል፡፡

እስራኤል በበኩሏ ትናንት በፈጸመችው ጥቃት 16 የሂዝቦላህ አባላት መግደሏን ገልጻ÷ ከነዚህ መካከልም 12ቱ የቡድኑ ከፍተኛ አዛዦች ናቸው ብላለች፡፡

እንዲሁም ሂዝቦላህ ባወጣው መግለጫ ደግሞ የቡድኑ ከፍተኛ አዛዥ ኢብራሂም አኪል በእስራኤል ጥቃት እንደተገደለበት አሳውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.