ግብርናችንን ለማሻገር በእውቀት ላይ መመስረት ይገባል – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ግብርናችንን እናሻግር ካልን በእውቀት ላይ የተመሰረተ የግብርና ልማት ስራ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የግብርና ልማት ጣቢያ ባለሙያዎችን የደረጃ ማሻሻያ ስልጠና አስመልክቶ ውይይት ተካሂዷል፡፡
ስልጠናው በግብርና ሚኒስቴር እና በስራና ክህሎት ሚኒስቴር ትብበር በተመረጡ የግብርና ኮሌጆች ይሰጣል ነው የተባለው፡፡
የስልጠናው አሰጣጥ ሂደቱም በደረጃ አንድ፣ ሁለት እና ሦስት በስራ ላይ የሚገኙ የልማት ጣቢያ ባለሙያዎች ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ ለማድረግ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ፥ ግብርናችንን እናሻግር ካልን በእውቀት ላይ የተመሰረተ የግብርና ልማት ስራ በመስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ላለው ውጤት ትልቅ አስተዋጾ እያበረከቱ ያሉትን የልማት ጣቢያ ባለሙያዎች ስልጠና ላለፉት ዓመታት የልማት ጣቢያ ባለሙያዎች ለሚያነሱት ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው ፥ ግብርናውን ለማዘመን በሰው ሃይል ላይ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሯ አክለውም ከዚህ ስልጠና ጎን ለጎን አርሶ አደሩንም ማሰልጠን የሚቻልበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠይቀዋል፡፡
በውይይት መድረኩ የግብርና እና የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ የክልል ግብርና ቢሮ አመራሮች፣ የግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች ኃላፊዎች መገኘታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡