የጊፋታ ታላቁ ሩጫ በወላይታ ሶዶ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጊፋታን በዓል ምክንያት በማድረግ “የጊፋታ እሴቶች ለሁለንተናዊ ብልፅግና ” በሚል መሪ ሀሳብ የሩጫ ውድድር ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ ወገኔ ብዙነህ፤ የጊፋታ እሴት የመቀራረብና የእርቅ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ከፋፋይ ነጠላ ትርክቶችን በመተው ገዢ የሆኑ ሀገራዊ ትርክቶችን ማፅናት ይገባል በማለት ገልጸው፤ በዚህ እሳቤ እንደ ሀገር በወንድማማችነት እጅ ለእጅ በመያያዝ ለሰላም ዘብ መቆም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ጴጥሮስ ወ/ማሪያም በበኩላቸው፤ የጊፋታ ታላቁ ሩጫ ማሕበራዊ መስተጋብርን በማጠናከር ለሀገራዊ የጋራ መግባባት አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
የዘንድሮው የጊፋታ በዓል ነገ እና ከነገ በስቲያ በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል።
በመለሰ ታደለ እና ኢብራሂም ባዲ