80 ካርቶን ሕገ-ወጥ መድሐኒቶች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ13 ሺህ 305 ዩሮ በላይ የሚገመት ዋጋ ያላቸው 80 ካርቶን ሕገ-ወጥ መድሐኒቶች በጋምቤላ ከተማ መያዙን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ገለፀ።
ህግ-ወጥ መድሐኒቶቹ የተያዙት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ማዕከል ኢንተለጀንስ ዋና መምሪያ ከጋምቤላ ክልል ፖሊስ የመረጃ አበላት ጋር ለሁለት ወር ባደረገው ክትትል ነው ተብሏል፡፡
በዚህም ሕገ-ወጥ መድሃኒቶች እና የሕፃናት ወተት በጋምቤላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በሁለት አምቡላንሶች ተጭነው ሲጓጓዙ እንደተያዙ ተገልጿል፡፡
በአካባቢው ለሚገኙ የውጭ ስድተኞች አገልግሎት የሚውል ነው በሚል ምክንያት ሕገ-ወጥ መድሃኒቶቹ ሕጋዊ ሽፋን እንዲያገኙ በሆስፒታሉ ገቢና ወጪ በማድረግ ለግል ጥቅማቸው ሊያውሉ የነበሩ ሁለት ሾፌሮችና ሁለት የህክምና ባለሙያዎች ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም ከነ-ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ሥር ውለው በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ጋምቤላ ቅርንጫፍ ምርመራ እየተካሄደ እንደሚገኝም የፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡