Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል በማልታና ለንደን ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሐበሻቪው ከማልታ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በማልታ ለመጀመሪያ ጊዜ፤ በካናዳ ደግሞ ለ5ተኛ ጊዜ የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል ሊያካሂድ ነው።

በፌስቲቫሉ ላይ በማልታ አፊኒ፣ ዓባይ ወይስ ቬጋስ እና ዝምታዬ የተሰኙ ፊልሞችን በሴንት ጀምስ ካሻሊየር ሲኒማ ከጥቅምት አንድ እስከ ጥቅምት 3፤ 2017 ዓ.ም ለእይታ እንደሚቀርብ ተነግሯል፡፡

በተመሳሳይ በለንደን ላምባዲናና አፊኒን በሪትዝ ሲኒማ ከጥቅምት 8 እስከ 10 እንደሚያሳይ ተጠቁሟል፡፡

ፊልሞቹ ለሀገራቱ ዜጎች፣ ለዘርፉ ባለሙያዎችና ለዳያስፖራው ማህበረሰብ አባላት እንዲሁም ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች ለእይታ የሚቀርቡ መሆኑም ነው የተገለጸው።

ሥነ-ስርዓቱ በውጭ ሀገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሀገራቸው ኪነ-ጥበብ ጋር ለማገናኘት ከሚፈጥረው ዕድል እንዲሁም ለኢንዱስትሪው ዕድገት ከሚኖረው ፋይዳ ባለፈ በዲፕሎማሲው መስክም በሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጎልበት ከፍ ያለ አስተዋፅኦ አለው ተብሏል።

መሰል መርሐ-ግብሮች ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ዓለም ሀገራት ሲዘጋጁ የቆየ ሲሆን ፥ ዘንድሮ አራት የኢትዮጵያ ፊልሞችን በማልታና ካናዳ ለእይታ ይቀርባሉ ተብሏል።

የፌስቲቫሉ አዘጋጅ ሐበሻ ቪው ድርጅት በቀጣይ የተለያዩ ሀገርኛ ፊልሞችን ወደተለያዩ ዓለም ሀገራት በመውሰድና በማስተዋወቅ ተወዳዳሪነታቸው ለማሳደግ የሚሰራ መሆኑን ስራ አስፈፃሚዋ ወ/ሮ ትዕግስት ከበደ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

በመራዖል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.