Fana: At a Speed of Life!

ኮሜሳ ድንበር ተሻጋሪ የኤሌክትሪክ ንግድን የሚያሳልጥና የሚያጠናክር ፕሮጀክት ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ድንበር ተሻጋሪ የኤሌክትሪክ ንግድን የሚያሳልጥና የሚያጠናክር ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል፡፡

በኮሜሳ አባል ሀገራት የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ትስስርና ንግድ የሚመራበት የሕግ ማዕቀፍና የታሪፍ ቁጥጥር ላይ ያተኮረ ዓውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ የኮሜሳና የምስራቅ አፍሪካ የሃይል ልማት ዘርፍ ከፍተኛ አመራሮች እና ኢትዮጵያን ጨምሮ የአባል ሀገራቱ ተወካዮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

መድረኩ በቀጣናው የሃይል ግብይት፣ ቁጥጥርና አስተዳደር የሚመራበትን ማዕቀፍ ለማዘጋጀት የተቋቋመው የጥናት ቡድን ያገኘውን ውጤት ለአባል ሀገራቱ የሚያቀርብበት መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በኮሜሳ የኢነርጂ ተቆጣጣሪ ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሞሃመዲን ኢ ሰኢፍ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ኮሜሳ በአባል ሀገራቱ መካከል የኢኮኖሚ ውህደትና ልማት እንዲፈጠር በትኩረት እየሰራ ነው፡፡

በአባል ሀገራቱ የኤሌክትሪክ ሃይል ንግድን ለማጠናከር የተጀመረው ፕሮጀክትም በቀጣናው ያለውን የሃይል ትስስር ይበልጥ እንደሚያሳድገው አስገንዝበዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በአፍሪካ ልማት ባንክ እና በኮሜሳ ትብብር በ1 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜረካ ዶላር ተግባራዊ እንደሚደረግ አንስተዋል፡፡

ይህም የቀጣው ሃይል ንግድ የሚተዳደርበትን የህግ ማዕቀፍ፣ የታሪፍ ሁኔታ እና ሌሎች የቁጥጥር ማዕቀፎችን በመወሰን የተሳለጠ የሃይል አቅርቦት እንዲኖር ያስችላል ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የኤሌክትሪክ ዘርፍ ቁጥጥር ዳይሬክተር ባህሩ ኦልጂራ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የታዳሽ ኢነርጂ ማዕከል ለመሆን በትኩረት እየሰራች ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከኬንያ፣ ሱዳንና ጅቡቲ ጋር የሃይል ትስስር እንዳላት ጠቁመው÷ በቀጣይ ከሌሎች የቀጣው ሀገራት ጋር ለመጀመር በሒደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ላላት የሃይል ትስስር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው÷ለተግባራዊነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል፡፡፡

የምስራቅ አፍሪካ የሃይል ልማት ዘርፍ ዋና ጸሃፊ ጀምስ ዋሆጎ÷ በአፍሪካ ለሚስተዋለው የሃይል አቅርቦት ውስንነት የመተዳደሪያ የሕግ ማእቀፍ፣ የታሪፍ እና የመሰረተ ልማት ችግር ዋናውን ድርሻ ይወስዳል ብለዋል፡፡

ኮሜሳ የሚተገብረው የሃይል አቅርቦት ትስስርና ንግድ የሚመራበት የሕግ ማዕቀፍ፣ የታሪፍ ቁጥጥርና አስተዳደርም ችግሩን እንደሚያቃልለው አውስተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.