በኢትዮጵያ የግልግል ዳኝነት ማዕከላት ተመዝግበው እንዲሰሩ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የሚገኙ የግልግል ዳኝነት ማዕከላትን ለመመዝገብና ስራ እንዲሰሩ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ፍትህ ሚኒስቴር እና ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት አፍሪካ በጋራ ያዘጋጁት 11ኛው የምስራቅ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ኮንፈረንስ “የግልግል ዳኝነት በአዲሱ ዘመን” በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡
በፍትህ ሚኒስቴር የፍትሐብሄር ፍትህ አስተደደር ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ንጉሴ ትዛዙ እንዳሉት፤ ኮንፈረንሱ የግልግል ዳኝነትን በአፍሪካ ከማሳደግ ባሻገር ኢትዮጵያን ለግልግል ዳኝነት ማእከልነት ምቹ መሆኗን ለማስተዋወቅ ያስችላል።
ኢትዮጵያ የግልግል ዳኝነትን የሚመለከተዉን የኒውዮርክ ኮንቬንሽ ስምምነት መፈረሟ ደግሞ የበለጠ ተመራጭ የግልግል ዳኝነት ማዕከል መዳረሻ መሆን እንደምትችል ለማሳየት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።
ሀገር ዉስጥ የሚገኙ የግልግል ዳኝነት ማዕከላትን ለመመዝገብና ስራ እንዲሰሩ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ዓለም አቀፍ ማዕከላት በኢትዮጵያ የግልግል ዳኝነት ቢሮ ከፍተዉ እንዲሰሩ ለማድረግ ኮንፈረንሱ እድል ይሰጣል ሲሉ አክለዋል፡፡
በኮንፈረንሱ ላይ የንግድ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ የመንግስት ባለድርሻ አካላት፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ከተለያዩ ሀገራት ተሳታፊ ሆነዋል።
መድረኩ በዘርፉ የሚሰሩ ባለሙያዎችን፣ የመንግስት ተወካዮችንና ባለድርሻ አካላትን የሚያገናኝ ሲሆን በአፍሪካ ቀጠናዊ ትስስርና እድገት ዙሪያ ምክክሮችና ገለጻዎች ይደረግበታል መባሉን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።