የመስቀል ደመራና ኢሬቻ በዓላት አከባበርን ለማስተባበር16 ሺህ ወጣቶች ተዘጋጅተዋል- ማህበሩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ለመስቀል ደመራና ኢሬቻ በዓላት አከባበር 16 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ለማስተባበር መዘጋጀታቸውን የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር አስታወቀ።
በመስከረም ወር በደማቅ ሥነ-ሥርአት ከሚከበሩት የአደባባይ በዓላት መካከል የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት ይጠቀሳሉ።
በእነዚህ በዓላት በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች፣ የበዓሉ አክባሪዎችና ታዳሚዎች እንደሚታደሙ ይጠበቃል፡፡
በዚሁ መሰረት ለበዓላቱ ሰላማዊ የአከባበር ሒደት ለአቀባበልና መስተንግዶ በርካታ የመዲናዋ ወጣቶች መዘጋጀታቸውን የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ዋና ጸሐፊ ይሁነኝ መሀመድ ተናግሯል፡፡
የኢትዮጵያ መገለጫና የዓለም ሃብት የሆኑትን የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት እሴታቸው ተጠብቆ በደማቅ ሥነ-ሥርአት እንዲከበሩ የበኩላችነን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ማለቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በሁነቱ ላይ እንግዶችን ለመቀበል፣ ለማስተባበርና ለማስተናገድ 16 ሺህ የማህበሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ዝግጁ መሆናቸውንም ነው ያመላከተው፡፡