ዩኒቨርሲቲው በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች የልሕቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራሁ ነው አለ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች የልሕቀት ማዕከል ለመሆን በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡
የዩኒቨርስቲው ም/ፕሬዚዳንት ተመስገን ወንድሙ (ዶ/ር) ÷ ተቋሙ ላለፉት ሰባት ዓመታት ትኩረቱን በሳይንስና ቴክኖሎጂ መስኮች ላይ በማድረግ ተማሪዎችን እያሰለጠነ ይገኛል ብለዋል።
በዋናነት በሳይንስ፣ በኢንጂነሪንግና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ሀገሪቱ የምትፈልገውን የሰው ሃይል ለማፍራትና እድገቱን ለማፋጠን እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዘርፉ ተማሪዎችን ተቀብሎ ከማሰልጠን ባሻገር የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና የሮቦት ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ በ8 መስኮች ላይ የልህቀት ማዕከል እየገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
የልሕቀት ማዕከሉ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በሮቦቲክ፣ በናኖ ቴክኖሎጂ፣ በማዕድን፣ በባዮ ቴክኖሎጂ፣ በኮንስትራክሽን ጥራት፣ በኒውክሌር ሳይንስ ዘርፎች ላይ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ያለ ቦታ ሊያሰጠውና አቅሙን ለማሳደግ በሚያስችለው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ በተለየ ትኩረት እየሰራ መሆኑንም ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡